የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ለጤና ባለሙያው የተጠናከረ የጤና ኢንሹራንስ ስርዓት እንዲኖር ለመስራት ከሚሹ ሁሉ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነው፡፡

ባለፉት ቀናት ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ሐኪሞች ሁሉም የአቅሙን ለማድረግ ሲረባረብ ተመልክተናል፡፡ በእውነት ፍጹም ኢትዮጵያዊ በጎነት የታየበት የአቅምን ብቻ ሳይሆን ያለውን የሰጠም ሰው ተመልክተናል፡፡ ይሁንና የነዚህን ሁለት ውድ ሃኪሞቻችንን ህይወት ከመታደግ በተጨማሪ በቀጣይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መሰረታዊ በሚባል ሁኔታ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችል ልክ መሰራት እንዳለበት ከታች ጀምሮ እሰከ እውቅ ፕሮፌሰሮች ድረስ ሃሳብ ሲሰነዘርበት በሐኪም ፔጅ ለመመልከት ችለናል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ከግል ተነሳሽነት በመነሳት ልዩልዩ ሃሳቦች በማምጣት እየተጉ ላሉ ተቋማትና ግለሰቦች ያለንን አድናቆት ሳንገልጽ አናልፍም፡፡ የግል ምልከታን በጽሁፍ ከመግለጽ በተጨማሪ ተቋማዊ በማድረግ ለመስራት መሞከሩ ደግሞ አፈጻጸሙን ለማፋጠን ሁነኛ መንገድ በመሆኑ ይህም የሚደነቅ መነሳሳት ነው፡፡

ማህበራችን በጤና መድህን ዙሪያ አስቀድሞም ባገኘናቸው አጋጣሚዎች ከሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ጋር በጉዳዩ ላይ ከመምከር በተጨማሪ የካምፔንና አድቮኬሲ ስልታዊ ዕቅድ በማዘጋጀት የተለያዩ የሙያ ማህበራትን በማስተባበር በርካታ ስራዎች እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም የሙያ ማህበራቱን በማስተባበር ለቀድሞው የጤና ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰን በጉዳዩ ለይ ለመምከር በደብዳቤ የስብሰባ ጥሪ አስተላልፈን ነበር፡፡ የስብሰባ ቀኑ በተወሰነልን ቀንም የሙያ ማህበራቱን ፕሬዝደንቶች በመያዝ በጉዳዩ ዙሪያ ከቀድሞው የጤና ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጋር እጅግ ውጤታማ ምክክር አካሂደናል፡፡ የጉዳዩን አሳሳቢነት ለማሳየት የሚረዳ መጠነኛ ጥናት በማቅረብ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ የገለጽን ሲሆን ከሳቸው ጋር ባካሄድነው ስብሰባ መጨረሻም ጉዳዩን ወደሁለተኛ ምዕራፍ የሚያሻግር ቡድን ተቋቁሟል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይህንን ጥረት ለመደገፍ የሚፈልግ ባለሙያ ካለ የተሻለ እና ሊፈጸም የሚችል ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ ስለሚረዳ ግብዣችንን ለማቅረብ እንወዳለን፡፡(ethiopianmed@gmail.com በዚህ ኢሜል ስምና ስልክ ላኩልን)

ከዚህ በላይ ከተገለጸው በተጨማሪ ማህበራችን በሃገራችን ኢትዮጵያ ለሚገኙ የተሻለ የመስራት አቅም አላቸው ተብለው ለተለዩ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደብዳቤ በመላክ በጋራ ለመስራት ጥሪ አቅርበን ነበር፡፡

ጥሪ ከቀረበላቸው ኩባንያዎች መካከል ልዩልዩ የፕሪምየም አማራጮች ይዞ ከመጣ አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ጋር የተሻለ መቀራረብ በመፍጠርና ልዩ ልዩ ስብሰባዎች በማካሄድ ለሕክምና ባለሙያው የተሻለ ፕሪሚየም በሚያስገኙ ዝርዝሮች ዙሪያ ድርድር በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡

አሁንም ቢሆን ፕሮፌሰር ብሩክ ላምቢሶ በሰጡት አስተያየት መሰረት ይህንን ጉዳይ ለመምራት ብቻ ሳይሆን ይመለከተኛል ከሚል በጎ ተጽዕኖ ለማምጣት ፈቃደኛ ከሆነ ማንኛውም አካል ጋር ለመምከር ብሎም ፍጻሜ ላይ እንዲደርስ ለመስራት ያለንን ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም ይህንን ሃሳብ በነጻነት እንዲንሸራሸር የሚዲያ ሃላፊነቱን እየተወጣ ለሚገኘው ሃኪም ፔጅ፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት የድርሻቸውን ከመወጣት በተጨማሪ ልዩልዩ ሃሳቦችን በማቅረብ ብዙ አካላትን ትኩረት እንዲያገኝ በማድረግ አስተያየት ለሰጣችሁ ባለሙያዎች በሙሉ በተለይም የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር አባላት ምስጋናችን ይድረሳችሁ፡፡

በህክምና ላይ ለምትገኙ የህክምና ባለሙያዎች በሙሉ ከያዛችሁ ህመም ድናችሁ ወደስራችሁ ትመለሱ ዘንድ መልካም ምኞታችንን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡