ዶ/ር ጎዳናህክምና የሳይንስ እውቀት ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ መራራትንና ህመሙን መጋራትን ይጠይቃል፡፡

ከዶ/ር ሽታዬ አለሙ ለታካሚ መራራትን ተምሬያለሁ

ዶ/ር ጎዳና ጃርሶ በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር እና የኢህማ በአዳማ ፕሬዝዳንት

የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ላለፉት 60 ዓመታት በሆስፒታልነት ሲያገለግል ቆይቶ በ2004 አዲሰ በወጣው የህክመና ትምህርት ስርዓተ ትምህርት New Innovative Medical Education 40 ተማሪዎችን ተቀብሎ ነው የህክምና ትምህርት ማስተማር የጀመረው:: የመጀመሪያ ተማሪዎቹንም በህክምና ዶክተርነት አስመርቋል ፡፡ ኮሌጁ ማስተማር በጀመረበት ወቅት ዶ/ር ጎዳና የመጀመሪያው ፕሮቮስት ነበር፡፡ 

# ሂሩት ተፈራ(ኢህማ)


ዶ/ር ጎዳና እና እኔ ስለ ቦረና ስለ ገዳ ስርዓትና ስለ ህክምና ካወራነው በትንሹ ላስነብባችሁ
በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት አንዳንድ ሰዎች ቅሬታ አላቸው አንተ ምን ትላለህ?
ዶ/ር ጎዳና- ስርዓተ ትምህርቱ ምንም ችግር የለበትም እንዲያውም ችግር ፈቺ ነው ስርዓተ ትምህርቱ ሲገመገምም ሆነ ሲጸድቅ ነበርኩ በበፊቱ ስርዓተ ትምህርት የሌሉ ትምህርቶች የተካተቱበት ነው ህክመና ክህሎትን የሚጠይቅ ነውና ከታካሚ ጋር የምንነጋገርበት ቋንቋችን የዳበረ የሚያሳምን መሆን አለበት የሙያ ስነምግባር ያለው እጁ የተፍታታ ሃኪም ነው መሆን ያለበት እነኚህ ሁሉ የየተካተተበት ነው፡፡
ተማሪዎቹም እንደማንኛውም ተማሪዎች ትምህረት የመቀበል ደረጃ ይኖራቸዋል…በእርግጥ ከስራ ስለመጡ ትንሽ ማህበራዊ ችግሮች ይኖራሉ፡፡
ተማሪዎቹ ከስራ መምጣታቸው የተለየ እገዛ አድርጓል ብለህ ታምናለህ?
ያየነው ነገር… አንድ ባች አስመርቀናል አጋጣሚውን ያላገኙና ሙያውን የሚወዱ ናቸው የተቀበልናቸው ስራ ላይ ሆነው ያለውን ክፍተትን አይተው ምን ማወቅ እንዳለባቸው ተረድተው ስለመጡ ቀጥታ ከሚገቡት generic ተማሪዎች የተሻለ ልምድ ኖሯቸው ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
ትምህርቱም self learning ማለትም problem based learning በመሆኑ ተማሪው የጤና ችግሮችን ከአገራችን ተጨባጭ የጤና ሁኔታዎች አንጻር ተረድቶ ለችግሮች መፍትሄን በመስጠት የሚማርበት በመሆኑ ውጤታማ ነን እላለሁ፡፡
ኮሌጁ በምን ደረጃ ነው ያለው?
ኮሌጃችን ከጥቂት ወራ በኋላ ለሁለተኛ ግዜ ያስመርቃል …በስፔሻሊቲም በ ቀዶ ህክምና፣ በህጻናት፣ በጽንስና ማህጸን እና በውስጥ ደዌ ህክምና ማስተማር ጀምሯል፡፡ የቀዶ ህክምናና የጽንስና ማህጸን ተማሪዎች Resident 3ኛ ዓመት ደርሰዋል ከአንድ አመት በኋላ እናስመርቃለን፡፡ በህብረተሰብ ጤና አጠባበቅም በማስተርስ ደረጃ ማስተማር ጀምረናል፡፡ ይሄ ደግሞ ለህብረተሳባችን የተሻለና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት መስጠት ችለናል፡፡
ያለው ህንጻ ይህን ሀሉ ተማሪ ማስተናገድ ይቻላል?
ማስፋፊያን በተመለከተ ኮሌጃችን በዩኒት ደረጃ ማለትም የአንጀት የኩላሊት የልብ ህክምናዎችን ለመስጠትም ሆነ ለማስተማሪያነት የሚያገለግል ሁለገብ ህንጻ 300 አልጋ ያለው ሆስፒታል በክልሉ መንግስት ተገንብቶ አልቋል… ለተመላላሽ ታካሚዎች የሚሆን ሁለተኛ ህንጻ አልቆ በቅርብ አገልግሎት ይጀምራል፡፡
ስራው ሙሉ በሙሉ ሲጀመር የአገልግሎትና የትምህርት አሰጣጥ ጥራት ጎን ለጎን ያሻሽላል ለአገሪቱም ብቁ ሃኪሞችን ማፍራት ይችላል ፡፡
ዶ/ር ጎዳና በልጅነቱ
በልጅነቴ ያው ጠጆች ስጠብቅ ነው ያደኩት… ትውልዴም እድገቴም ቦረና ህብረተሰባችን አርብቶ አደር ስለሆነ ጥጆች ስንጠብቅ ነው ያደኩት የትምህርቱ ነገር በኋላ ላይ ነው የመጣው መጀመሪያ ብዙ ከብቶች እንዲኖሩን እንዴት መንከባከብ እንዳለብን ነው የምንማረው…
በቦረና ባህል በተለይ ወንድ ስትሆን ሃላፊነት ይኖራልና እንዴት ወደ ትምህርት ቤት ልትገባ ቻልክ?
ልክ ነሽ በኛ ባህል ወንድ ልጅ ከልጅነቱ ጀምሮ ሃላፊነት አለው እኔ 5ኛ ልጅ ስለነበርኩ ነው፡፡ አባቴም ለትምህርት ጥሩ አመለካከት ነበረውና አንድ እሱ ይማር ብለው ለሙከራ ነበር ያስገቡኝ …መግባት ብቻ ሳይሆን መቀጠል ይቻላል ወይ የሚለው ነው ወሳኙ…ያን ግዜ ከባድ ነበር የምማርበት ት/ቤት 20 ኪሎ ሜትር ጠዋትና ማታ መጓዝና ጫካ አቋርጦ መሄድ ይጠይቃል… ሳይገፉበት ያቋረጡም አሉ፡፡ እኔ አባቴ ጠዋትና ማታ እያመላለሰ ነው ያስተማረኝ በኋላም አዳሪ ት/ት ቤት ገብቼ ነው ሃይስኩል የጨረስኩትና ኮሌጅ የገባሁት፡፡
አባቴ አልገባውም እንጂ አብሮኝ ክፍል ቢገባ እሱም ኮሌጅ ይገባ ነበር.. ረጅም ሳቅ
አዳሪ ትምህርት ቤት እንዴት ለቀቁህ?
ቦረና ውስጥ ልጆች ነጻነት አላቸው ይደመጣሉ ይሄ ተመችቶኛል ይሄ ጥሩ ነው ካልሽ ካንቺ የሚጠበቀው ማስረዳት ብቻ ነው.፡፡ ከአባቴ ጋር ስለትምህርቴ እናወራ ነበር.. አባቴን አስረዳው ነበር ያው አንዳንዴ የቀለም ትምህርት ግራ የሚያጋባሽ ግዜ ይኖራል… አንድ ቀን አባቴን ይሄ ትምህርት ምንም አልገባኝም የማይሆን ነገር ነው አልኩት፡፡ እንዴት አለኝ
አስተማሪዎቹ ጸሃይ ሳትሆን መሬት ነች የምትዞረው ይላሉ ይሄ ነገር አልገባኝም እኔ የማየው ጸሀይ ስትዞር ነው አልኩት .. በቦረና ብዙ ከህብረተሰቡ የምትማሪው ነገር አለ አዲስ ሃሳብ ስታመጪ ማስረዳት አለብሽ… ግን በክፉ አልታየም ማሳመን ነበረብኝ እኔም አስረዳኋቸው
ያንተ ቤተሰብ በገዳ ሃላፊነት አልፏል?
አዎ…ባጋጣሚ የኛ ቤተሰብ በወቅቱ ሃላፊነቱን ስለጨረሰ ብዙ ሃላፊነት አልነበረንም በአማካሪነት ነበር የሚሰራው..ለዚህም ነው ወደ ትምህርቱ የገባሁት እንጂ በገዳ ስርዓት ሃላፊነት የሚሰጥሽ ከልጅነት ጀምሮ ነው..ደበሌ ከሚባለሁ እድሜ እስከ ራባይ ደረጃ ድረስ ሃላፊነት አለብሽ ያንን አልፎ ትምህርት መግባት አታስቢውም፡፡

ስለ ገዳ ስርዓትና ልጅነት ትንሽ ንገረኝ

በቦረና አንድ ልጅ ሲወለድ ከየትኛው መስመር (ጎጌሳ ነው የሚባለው) እንደተወለደ ቤተሰቡን ዘሩን እስከ 12 ድረስ ማወቅ አለበት በዚህ ነው የምትመሪው ጋብቻም ሃላፊነቱም በዚህ ነው የሚወሰነው ሁሉም ሰው ማወቅ አለበት 5 ሃረግ ነው በቦረና ያለው እሱን ማጥናት ይኖርብሻል 
በደበሌ እድሜ ዘርሽን በቃል ታጠኛለሽ ከጎን ያሉ ዘሮችሽን ትቆጥሪያለሽ… በኛ ወንድም የሚባለው በደም ስለተወለድሽ ብቻ ሳይሆን ሉባ የሚባል አለ በሉባ እንደ ወንድምና እህት ትተያያለሽ እንደ አባትና ልጅም ትተያያለሽ …ስለዚህ ከጎን ማን ይዛመድሃል የሚለውን ሁሉ ትማሪያለሽ፡፡ ገዳን ይዞ ያለው ሰው ገዳውን ሲጨርስ ልጆቹ ይቀጥላሉ በ 8 ዓመት እየተከፋፈለ ለ 40 ዓመት አንድ ቤተሰብ ይቆያል፡፡
አባ ገዳ አንድ ሰው ይሁን እንጂ ገዳው የሚመራው በካውንስል ነው በገዳ ውስጥ ሃላፊነት ዝም ብሎ አይሰጥም ተወዳድረሽ ብቁ መሆንሽ ከታመነ ብቻ ነው፡፡ ያ የገዳ ቤተሰብና ቡድኑ ግዜው ሲያልቅ ሁሉም አንድ ላይ ይወርዳል ሌላው ደሞ ይተካል፡፡
ስንት ከብቶች ነበሯችሁ?
ሳቅቅ ..በኛ እነኳን የከብት ቁጥር የልጆች ቁጥርም አይነገርም…ምንም ከብት የሌለው ሰው ሚስቱ ብትወልድ ወተተን የሚወስደው እሱ ነው… በቦረና ለሴቶችና ለህጻናት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡
አንዲት ላም ስትወልድም ጥጃውን እንዲሁ ለሌላ ሰው ነው የሚሰጠው… ይገባኛል ብሎም መጠየቅ ይችላል፡፡ የኔ ብቻ የሚባል የለም ልጆችም እንዲሁ በዘር ሃረግም ሆነ በሉባ አንዱ የሌላው ልጅ ሊሆን ይችላል፡፡
ስለ ቦረና እና ስለ ገዳ ለመጻፍ ብዙ ጨዋታንንና ግዜን ይጠይቃል በጣም ነው ተማርኬ ሳዳምጥ የነበረው፡፡
ከቦረና ቀጥታ ጎጃም አልከበደህም?
ረጅጅጀም ሳቅ.. የሚገርምሽ ባህርዳር የት እንደሆነ ማስረዳት በራሱ ጭንቅ ነበር እንግዲህ እኔ የምሄደው በጣም ዝሩቅ ሃገር ነው ብዬ ተናገርኩ …አንድ ከባህርዳር የመጣ የኛን ያህል ባህርዳር የጠፋችበት ሰው ነበርና እሱን ለመጠየቅ ሄድኩ ና እንዴት መሄድ እንዳለብኝ ነገረኝ በቃ…ስልከ የለ የሚቀበልሽ ዘመድ የለ…
ባህርዳር እንደደረስኩ ሬጂስትራር ልመዘገብ ቆሜ ስምህ ማነው ስትለኝ ጎዳና አልኳት 
ጎዳና? አለችኝ 
አዎ ጎዳና 
ከየት ነው የመጣኸው? 
ከቦረና 
ቦረና የት ነው አለችኝ …ቻሌንጁ ከዚህ ይጀምራል እንግዲህ አሀንም ረጅም ሳቅ

ግን ጎዳና ማለት ትርጉም አለው

አዎ ጎዳና የተባልኩት ያው የኛ ማህበረሰብ አርብቶ አደር ነው …ለግጦሽ ፍለጋ መዟዟር ይኖራል ያ ልምድ ጎዳንሳ ነው የሚባለው…እንግዲህ ለግጦሽ ፍለጋ በተወጣበት ወቅት መሰለኝ የተወለድኩት …ጎዳንሳ ከሚለው ነው ጎዳና የመጣው፡፡
ባህር ዳርና ጎንደር ”ጎዳናው” እየተባልኩ ነው ስጠራ የኖርኩት…በራሱ እየቀለደ

ሌላው የከበደኝ አማርኛ ነበር በቦረና አማርኛ ብዙም አንሰማም… ማር ለመሸመት ስወጣ እቸገር ነበር ይፈጥኑብኛል እኔም ቋንቋዬ ይከብዳቸው ነበር፡፡ የአምሳሉ አክሊሉን ዲክሺነሪ እያነበብኩ ድሮ ያጠራቀምኩትን አንዳንድ ቃላት ሰባስቤ በ6 ወር ውስጥ ጥሩ ተናጋሪ ሆንኩ፡፡
የአማርኛ ባር ውስጥ ገባህበታ
አዎዎ ዶርም ጓደኞቼም ከተለያየ ቦታ የመጡ ናችው እንዲያውም ከሌላ አገር የመጣን ነው የሚመስለው ልዩነተ እንዳለ ሁሉ ጥሩ ነገርም ነበረን.. ጎንደርም 6 ዓመት ስማር ተደስቼ ብዙ ነገር ተምሬ ነው የወጣሁት እዚያውም ለመቅረት ፈልጌ ነበር ተመችቶን ነበር ከቤተሰብ መራቅ ሆነብኝና ተመልሼ ወደቦረና ተመለስኩ እንጂ፡፡
ለዛሬው ማንነቴ ጎንደር ትልቅ አስተዋጾ አለው ጎንደርን ህዝበን እወደዋለሁ ደግ ነው፡፡
የቦረና ምኑ ይናፍቅህ ነበር?
ወተት…ወተት እየጠጣን ነው ያደግነው…ለመጀመሪያ ግዜ ሻይ ቤት ለመጠጣት ሄጄ ጣእሙን ሳልወደው ተውኩት… ወተት ባጣም ነበር የሚናፍቀኝ፡፡ እኛ ጋ እኮ ወትትን ለማጣፈጥ የማይደረግ የለም
ቆራሱማ?
አዎ ቆራሱማ ይደረጋል( ቆራሱማ በወይራ ማጠን ነው)
ህክምናን ስትመርጥ ቤተሰብ ምን አለ

ከዶ/ር ጎዳና ጋር ማውራት እሱም ሲያወራ ማዳመጥ አይሰለችም የሚያውቀው ያውቀዋል ቁም ነገር ላይ ረገጥ እያደረገ ስለራሱ ሲያወራ ቀልድ እየፈጠረ ለ አንድ ሰዓት ያህል ነው አብረን ቆየነው በተለይ የቦረናና የገዳ ስርዓትን ሲተርከው አፍ ያስከፍታል ማቆም አለብኝ…ሃኪም ጋ ጊዜ በጣም ውድ ነው ለምን ታካሚ ውጪ ይጠብቃላ
ካለችው የእረፍት… እረፍት ባልለውም ግዜውን ተሻምቼ ነበርና መሃል ላይ ልቀጥል ወይስ? አልኩት እያመነታሁ…ማታ ደግሞ ክሊኒክ አለ! እዚያም ታካሚ አለ!
እንቀጥል አለኝ ከሙሉ ፈገግታውና አክብሮቱ ጋር
ህክምናን ስትመርጥ ቤተሰብ ምን አለ?

ዶ/ር ጎዳና፡ በጣም ነው የተደሰቱት ምክንያቱም …ሃኪም በየትኛውም ህብረተሰብ የሚከበር ነው ትልቅ ሃላፊነትም ነው ያለበት የኛ ማህበረሰብ ደግሞ ከልጅነት ጀምሮ ሃላፊነትን ተቀብለሽ የምታድጊው አንዱ የገዳ ስርዓትም ነው…ከነሱ አልፌ ሃላፊነትን መውሰድ በመቻሌ በጣም ነው ተደሰቱት፡፡
ለምረቃ ቤተሰብ ይመጣል ያንተስ ቤተሰብ?
ወንድሞቼ መጥተዋል…በጣም ነው ተገረሙት ብዙ ዘመድ አፍርቼ በየቤቱ ድግስ ተደረጎ ስንጠራ በጣም ነው የተደሰቱት… እንደዘመድም ይጠያየቁ ነበር… በጣም ደስይላል
የት ነው ስራ የጀመርከው
ዶ/ር ጎዳና፡ ነጌሌ ቦረና ሆስፒታል ነው ጀመርኩት…
በምርጫህ ነው;
አዎ በምራጫዬ ነው… ምክንያም እኔ የገጠር ልጅነኝ የገጠሩ ህዝብ ደሞ ብዙ ነው ሪያሊቲውን በደንብ ነው የማውቀው ከተማንም ገጠሩንም ያከመ ሃኪም ነው መሉ ሃሪም ብዬ አምናለሁ ቻሌንጆችንም መጋፈጥ ማየት ነበር የምፈለልገወው…በወቅቱ ሃኮም እንደ አሁን አልነበረም በፈረንጆች 2005 ሱናሚ የተከሰተበት ነበር…ሜዲካ ዳይሬክትረር ነበርኩ ሃኪምም ነበርኩ ኢመርጀንሲ ቀዶህክምና ሰልጥኜ ነበር ቀዶ ህክክናም እሰጣለሁ፡፡ቦረና ውስጥ የምትሰሪውን ነገር ማስረዳት አለብሽ ተወልጄ ያደኩበት ስለሆነ በደንብ 
ከቦረና ካንተ በፊት ሃኪም ነበር?
ዶ/ር ጎዳና፡ የለም…ሃኪም መሆን አይደለም ሃይስኩል መጨረስም ችግር ነው
በሌላ ፊልድ ይኖራል በህክምና ግን አልነበረም…
አሁን ብዘ ናቸው እኔ የማማክራቸው እንደ እኔ ስፔሻሊቲ የሰሩ አሉ፡፡
ቀዳሚ መሆን ደስ አይልም?
በጣም ጥሩ ነው …ቻሌንጁ እንዳለ ሆኖ ነገሮች ተለውጠው ስታዬ ደስ ይላል… በቁጥር ብቻ አይደለም አንድም ሰው ሆኖ ለውጥ ማምጣት ይቻላል..ህብረተሰባችን ደግሞ ምክንያታዊ ሆነሽ ስትቀርቢ ያምኑሻል.. አሁን እኮ አባቶች ከብቶች እየጠበቁ ልጆቻቸውን ትምህር ቤት ማስገባት ጀምረዋል… 
አዲስ አበባ መቼ መጣህ?
ዶ/ር ጎዳና፡ 2007/8 ወቅተ የሚሊኒየም ሰኤች አይቪ ካምፔይን በኦሮሚያ ጤና ቢሮ ገብቼ ሰረሁ…ከባልደረቦቼ ጋር ኢትዮጵያን ዞርኩኝ በፈቃደኝነት እንዲመረመሩና ኮሚኒቲ ኮንቨርሴሽን ላይ ሰራን ውጤታማ ነበርን
ከዚያ በኋላ የውስጥደዌ ስፔሻሊቲ ገባሁ
ከጎንደር አስተማሪዎቼ የተማርኩት ህክምና የሳይንስ እውቀት ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ መራራትንና ህመሙን መጋራትን ነው፡፡ሳይንስ ቢራቀቅም መሳሪያዎች ማሽኖች በሽታውን መረምራሉ እንጂ እንደ ሰው አይራሩም አይጨነቁም ከጎንደር የተማርኩት መራራትን ነው አሁንም የማስተምረው ይህንኑ ነው፡
ከአስተማሪዎችህ ለይተህ የምታደንቀው?
ደ/ር ጎዳና፡ የምታደንቂያት በይልኝ…አንድ ስላልሽኝ እንጂ ሁሉም የየራሳቸው የሚደነቁበት አላቸው አንድ ካልሽኝ ግን ዶ/ር ሽታዬን ነው የምጠራው
ፕሮፌሽናሊዝምንና ለታካሚ መራራትን በተግባር ያስተማረችኝ እሷ ናት….
የአስተማሪዎቻችንን ውለታ የምንከፍለው እኛም ለሌሎች ጥሩ ሆኖ መገኘት ነውና የማምንበትም የማስተምረውም ይሄንኑ ነው 
CRC person means Dr. Godana ,…. Keep it up Dr. ኮሜንት ከሰጡት ውስጥ አንዱ
ዶ/ር ጎዳና …ሃኪም ሃብታም ነው
ረጅም ሳቅ…ሃበት በምን ይገለጻል እሰራሰ ሌላ ጥያቄ ነው
ሃበት በገንዘብና በማቴሪያል ከተለካ አዎ ሃሪም ደሃ ነው በእኔ እይታ ግን ሃብታም ነው ብዙ ሃብት ካላቸው ሰዎች የማይጠበቅ ሃላፊነት ከሃኪም ይጠበቃል …

የሰው ህይወት በእጀ ስላለ
አዎ… የሰው ህይወትን ሃላፊነት መውሰድ ትልቅ ሃብት ነው…ሰውን የሚረዳበት እውቀትና ክህሎት ስላለው ይሄም ትልቅ ሃበት ነው
ሃብታም ናቸው ትባባላችሁ
ምናልባት ህብረተሰቡ ሃኪሙን ያስቀመጠበት ቦታ ነው…ግን ሃኪም ሰርቶ ተፍጨርጭሮ እንደማንኛውም ሰው ገንዘብ ሊያገኝ ይችላል … አንዳንድ ሃኪሞችን ሳይ ህብረተሰቡ ካስቀመጠው ቦታ በጣም የወረደ ኑሮ የሚኖር ሃኪም አለ … ለምሳሌ አዳማ ሆስፒታል ዲዩቲ አምሽቼ አዲስ አበባ ቤቴ ልገባ ስል ተዘግቶብኝ የተመለስኩበት ግዜ አለ፡፡ 
ኖ እንደዚያ አይደለም!
እኔ እንዲያውም የማስበው ሃኪም ሃብታም ለመሆንና ቤትና መኪና ፍለጋ ከሚንከራተት እሱን የሚያገኝበት ሁኔታ ተመቻችቶ እሱ ሰውን ማዳን ስራ ላይ ብቻ ቢያተኩር እላለሁ፡፡ ምክንያቱም አንዱ የሃኪሙን ሃሳብ የሚሸረሽረው ወይም ደሞ ከሃገር የሚሰደደው አንዱ ምክንያት ይሄ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ዶር ጎዳና ጃርሶ ከኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዳለው አውቃለሁ በማንኛውም የማህበሩ ስብሰባ ይገኛል፡፡ ማህበሩ አቅም የሚያበጅበትን የሚሰፋበትን ገንቢ አስተያየት ጠንከር አድርጎ ነው የሚናገረው ፡፡ 
ይህን ቃለመጠይቅ ሳደርግለት…ለምን አንተ በአዳማ የማህበሩ ፕሬዝዳንት አትሆንም ብዬው ነበር 
ደስ ይለኛል…ግን ጉባኤው ነው የሚወስነው አለኝ
በማግስቱ የሱን መመረጥ ባልጠራጠርም የነበረው ሃኪም በመሉ ድምጽ አስመረጠው፡፡
አሁን ተራው የሱ ሆኑ በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአዳማ ቅርንጫፍ የኢህማ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ሆኖ ከኮሚቴው ጋር አብሮ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ ነው… በዚህ አንድ ወር ብቻ የደም ልገሳና አዳማን አረንጓዴ እናድርግ ብለውም በማህበሩ ስም ሲያስተባብር ከርሟል፡፡ 
ለዶ/ር ጎዳና ጃርሶ እና ለኮሚቴው መልካም የስራ ዘመን እንዲሆን እንመኛለን!