የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር በሃገራችን የሚገኙ የህክምና ትምህርት ቤቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ተቋም ለመገንባት ግልጽ ዕቅድ አውጥተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳሰበ፡፡

በሃገራችን የሚገኙ የህክምና ትምህርት ቤቶች የተሳተፉበት እውቅና አሰጣጥ (Accreditation) ዙሪያ የሚመክር መድረክ የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አባባ ተካሄደ፡፡

በመድረኩ የተገኙት በጤና ሚኒስቴር የጤና ዘርፍ የሰው ሃብት ልማትና ማሻሻያ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰግድ ሳሙኤል የሕክምና ትምህርት አሰጣጥ ጥራት እንዲኖረው ለማድረግ ተገቢውን ኃላፊነት መወጣት የሚጠይቅበት ጊዜ በመምጣቱ ሁላችንም የምንጋራው ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡ ይህን ማድረግ የራሳችንን እና ማህበረሰባችንን ጤና ለማስጠበቅ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ያሉብንን ክፍተቶች ፈተን ጥራት ያለው የትምህርት አሰጣጥን መሰረት በማድረግ ልዩ ልዩ ስራዎች መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ዱንካና ነጉሳ የኢትዮጵያ የትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ባስተላለፉት መልዕክት የሕክምና ትምህርት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል ከዚህ በፊት የነበሩ ተግዳሮቶችን በቁርጠኝነት በመወጣት እውቅና አሰጣጥ (Accreditation) ስርዓቱ በቅርቡ ለመጀመር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀው ተቋማትም እውቅናውን ለመውሰድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም ‘የእውቅና መኖር ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት ጥራትን እንደሚያረጋግጥና ማህበረሰቡ ለህክምና አገልግሎት ያለውን አመኔታ እንደሚጨምር ተጠቁሟል።”

ዶ/ር ተግባር ይግዛው የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ፕሬዝደንት በበኩላቸው በሃገራችን የሚገኙ የህክምና ትምህርት ቤቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ተቋም ለመገንባት መሳካት የሚያስችል ግልጽ ዕቅድ አውጥተው እንዲሰሩ ለማድረግ ይህንን የምክክር መድረክ ማህበሩ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ አክለውም የህክምና ትምህርት ቤቶች የስራ ኃላፊዎች ይህንን ከማስፈጸም አንጻር ያላቸው ጥያቄ እና አስተያየት ላይ በሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል ምክክር መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የሁሉም ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ክፍል እና የትምህርት ጥራት ኃላፊዎች በዚህ መድረክ ላይ በመገኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ዶክተር ተግባር በንግግራቸው ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ተቋማቱ የእውቅና አሰጣጥ ስራውንም የተሳካ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጣ ያላቸውን እምነት አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።