የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ከአክሃን የኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በሌሎች የክልል ከተሞች ለሚገኙ የህክምና ባለሞያዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለማናከናወን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙ ይታወቃል፡፡
ማህበሩ የመግባቢያ ሰነዱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እና የህክምና ባለሞያውን የቤት ባለቤት ለማድረግ በተያዘው እቅድ ላይ በተለያዪ ደረጃ ከሚገኙ የመንግስት አጋር መስሪያ ቤቶች ጋር የሚያደርገውን ውይይት ለአባላቱ እና ለህክምና ባለሞያው ለማሳወቅ ቃል በገባው መሰረት ከጤና ጥበቃ ሚኒስተር እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገንቢ የሆኑ ውይይቶችን አድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት ከጤና ጥበቃ ሚኒስተር ጋር በተደረገ ውይይት ሚኒስተር መስሪያ ቤቱ ማህበሩ የህክምና ባለሙያውን ጥቅምና መብት ለማስከበር የሄደበትን መንገድ በማድነቅ ለፕሮጀክቱ መሳካት ለማህበሩ ና ለኮንስትራክሽ ድርጃቱ ሙሉ በሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል፡፡
በተመሳሳይም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን በማህበሩ ለተነሳው ሃሳብ እውቅና በመስጠት እና በቀጣይ የከተማ አስተዳደሩን መሬት ለውጭ ድርጅቶች መስጠት ህጉ ስለማይፈቅድ በኢትዮጵያ ህክምና ማሀበር አማካኝነት የመሬት አቅርቦት ለማድረግ እንደሚቻል አሳውቀው፤ በቀጣይ ለሚከናወኑ ስራዎችም ከከተማ አስተዳደሩ ሙሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ይህ ፕሮጀክት እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ትልቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ በቀጣይም ስራውን በዋና አጋርነት አብረውን ለሚሰሩ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፣የጤና ጥበቃ ሚኒስተር እና የማህበራችን የሚዲያ አጋር ለሆነው ለአፍሪ ሄልዝ ቴሌቭዥን የከበረ ምስጋናውን ያቀርባል።