የኢትዮጵ ህክምና ማህበር በጤና ሚኒስቴር በኩል በመዘጋጀት ላይ የሚገኘው የጤና ባለሙያዎች ምዝገባና የሙያ ስራ ፍቃድ አሰጣጥ ላይ ተሳትፎ ያላደረገበት መሆኑንና መመሪያው ስራ ላይ በሚውልበት ወቅት ሙያውን የሚቃረን ሆኖካገኘው ተቃውሞውን እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገመቺስ ማሞ ዛሬ ነሐሴ 1/2011 ዓ.ም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዚሁ በመዘጋጀት ላይ በሚገኘው መመሪያ ዙሪያ ስብሰባ ለማድረግ በጠራው ስብሰባ ላይ ማህበሩ መመሪያውን የማይቀበልበትን ምክንያት አሳውቀዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ከቀናት በፊት ለማህበሩ በመመሪያው ላይ አስተያየት እንዲሰጥበት ለማህበሩ የተላከት ሲሆን ይህንንም ተከትሎ አባላቱ አስተያየት እንዲሰጡበት መላኩ ይታወሳል፡፡
በሚኒስቴር መስሪቤቱ በተዘጋጀው በዛሬው ውይይት ላይ ማህበሩ በፕሬዝዳንቱና የማህበሩ አንድ ሰው እንዲሳተፍ በደረሰው ጥሪ መሰረት ቢገኝም ስብሰባውን አቋርጦ ለመውጣት ተገደዷል፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ስብሰባውል ለማቋረጥ የተገደዱበትን ምክንያት ናቸው ያሉትን እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡
- የሞያ ፈቃድ በተመለከተ ከድሮም ጀምሮ መሰራት ያለበት በሞያ ማህበራ እንጂ በጤና ሚኒስቴር መሆን እንደሌለበት በማመን ለሚኒስቴር መስሪያቤቱ ባለስልጣናትና ሃላፊዎች በተደጋጋሚ አሳውቀቋል፡፡ በተመሳሳይ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ላይም በመግለጽና እንዲሁም ለጠ/ሚሩ ባስገባው የአቋም መግለጫ ይህንኑ በግልጽ አሳውቋል፡፡
- የጤና ሚኒስቴር የጤና ባለሙያዎችን በተመለከተ የሚወስዳቸው ተደራራቢ የሆኑ ሃላፊነቶች ማለትም ጤና ሚኒስቴር እራሱ መልማይ ፤ አስተማሪ ፈቃድ ሰጪ፤ ቀጣሪ፤ ጥራት ላይ ከሳሽ ፤ ቀጪም የሚሆነው ነገር አግባብ አለመሆኑን ይህም የጥቅም ግጭት የሚያስከትል እንደሆነና ይሄ መቅረት አለበት የተወሰኑ ስራዎችን ለሌላ እራሱን የቻለ ገለልተኛ ክፍል ወይም ደግሞ በሞያ ማህበራ መሰራት አለበት ብሎ ማህበሩ ሲከራከር የነበረው ጉዳይ ነው፡፡
- ለዚህም እንደመፍትሄ ከጎረቤት ሃገራትና ከሰለጠኑ ሃገራት ልምድ በመውሰድ የህክምና ት/ቤትንና የህክምና ተመራቂዎችን የሙያ ምዘናና ብቃት አፈጻጸም በተመለከተ መስጠት የሚገባው ራሱን የቻለ ካውንስል መሆን አለበት በማለት ይሄንን ሊሰራ የሚችል የኢትዮጵያ ዶክተሮች ካውንስል ፤ የጥርስ ሃኪሞች ካሉበት ደግሞ Ethiopian Medical & Dental Doctors Council በሚል በጥልቀት የተጠና ዶክመንት ለሚኒስቴር መስሪያቤቱ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡
- የሀኪሞቻችንን ችግር የጤና ሚኒስቴር መፍታት ካለበት ሀኪሞችን ከሚወክለው ማህበር ጋር ነው እንጂ በሌላ ሞያ ውስጥ ባሉ ሰዎች አንድ ላይ ተደርጎ መነጋገር የለበትም ፡፡ በዚህ የሞያ ፍቃድ ስብሰባ ላይም መነጋገር ካለብን ሃኪሞች እንደ ሃኪም ተሰብስበን ስለሃኪሞች የሞያ ፍቃድ እንነጋገራለን እንጂ ከሌሎች የሞያ አጋሮቻችን ጋር በመሆን አይደለም የምንነጋገረው፡፤ ይሄ ደግሞ ለሁሉም መስራት አለበት የሚል ጠንካራ አቋም ነው ያለን፡፡ ይሄንን ገልጸንላቸዋል፡፡ ይሄም ደግሞ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ሲያራምደው የነበረው አቋም ነው፡፡
ይሁን እንጂ ጤና ሚኒስቴር በሀኪሞቻችን ትጋት ጥራትና ስብእና አምኖ ይህንን መመሪያ የማውጣቱን ሃላፊነት ለኢትዮጵያ ህክምና ማህበር የሚሰጥ ከሆነ ማህበሩ የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የመንግስትንም ጥቅም ባልነካ መልኩ አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ የሞያ ምዘናና የብቃት ማረጋገጫ መመሪያ እንደሚያወጣ በመናገር ራሱን ከስብሰባው አግልሎ ወጥቷል፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገመቺስ እንዳሉት ከላይ የተዘረዘሩት ተግባራዊ እስካልተደረጉ ድረስ ከዚህ በፊት ከነበረው ነገር የተለየ ነገር አይሆንም፡፡ በቅርቡም የሃኪሞችን እንቅስቃሴ ከጫሩት ምክንያቶች መካካል አንዱ ይሄ ነው፡፡
እንደ ማህበርም ሆነ እንደ ግል ሃኪሞቻችን ሲያነሱት ከነበረው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ጥራትና ብቃትን በተመለከተ ነው፡፡ ስለዚህ ጥራትን መወሰን ያለበት የሙያው ባለቤት እንጂ መንግስት መሆን የለበትም ፤ ካልሆነም ደግሞ ገለልተኛ የሆነ አሰራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ የሚል አቋም ማህበሩ እንዳለው በእለቱ አሳውቀዋል፡፡